የባህል ስፖርት እንቅስቃሴ በክልሉ እንዲላመድና እንዲስፋፋ በክልሉ መንግስት ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እየተሠራ መሆኑ ተመላከተ ዱራሜ፣ ሚያዝያ 29/2018 ዓ.ም በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ወጣቶችና ስፓርት ቢሮ አዘጋጅነት ለ10 ቀናት የሚቆይ የባህል ስፓርቶች ሁለተኛ ደረጃ የዳኝነት ስልጠና ወራቤ ከተማ ላይ መሰጠት ጀምሯል።
አቶ ሰይፈ ዓለሙ የክልሉ ወጣቶችና ስፓርት ቢሮ ምክትል ሀላፊና የስፓርት ዘርፍ ኃላፊ ስልጠናውን በከፈቱበት ወቅት እንደተናገሩት የባህል ስፖርት እንቅስቃሴ በክልላችን እንዲላመድና እንዲስፋፋ የክልሉ መንግስት ልዩ ትኩረት ተሠጥቶ እየተሠራ ነው ። ስፓርቱን ለማስፋፋትና ለማሳደግ ከሚሰጡት ስልጠናዎች አንዱ የባህል ስፖርቶች የዳኝነት ስልጠና መሆኑን ያመለከቱት ሀላፊው፣ ይህም ስልጠና የዳኞችን ደረጃ ለማሳደግ ተብሎ እንደተዘጋጀ አብራርተዋል። ስልጠናው አዳዲስ ህጎች፣ ደንቦች፣ መመሪያዎች እንደሚችሉ ያስታወቁት አቶ ሠይፈ፣ የባህል ስፖርቶች ውድድርና ፌስቲቫሎችን ፍጹም ሰላማዊ፣ ፍትሃዊ በሆነ መልኩ መዳኘት የሚያስችል አቅም እንደሚፈጥር አብራርተዋል።
ከዚህ ባሻገርም ስልጠናው የዳኝነት ጥራትን ለማስጠበቅ እንደሚረዳና ያመለከቱት ምክትል የቢሮ ሀላፊው፣ ሰልጣኞች ከስልጠናው በኃላ ወደ አካባቢያችሁ ስትመለሱ የስልጠናውን ግብዓቶች ተግባራዊ እንድታደርጉ እጠይቃለሁ ብለዋል። በተጨማሪም የክልሉ ወጣቶችና ስፓርት ቢሮ እንዲሁም የክልሉ የባህል ስፓርቶች ፌዴሬሽን ለዘርፉ ዕድገት የተጠናከረ ድጋፍና ክትትል እንደሚያደርጉ ተናግረዋል። በመክፈቻ ስነ ስርዓቱ ላይ የክልሉ የባህል ስፖርቶች ፌዴሬሽን ስራ አስፈፃሚ አባል አቶ አልያስ ጭነሾ ተገኝተዋል።