Skip to main content
youthnews9

ወጣትነት የፈጠራና የእውቀት ምንጭ በመሆኑ ወጣቶች በስነ-ምግባር ታንጸው ለሀገር እድገት የበኩላቸውን እንዲወጡ በትኩረት ይሰራል፦ አቶ ጌታቸው ሌሊሾ 

ዱራሜ መጋቢት 08/2018 ዓ.ም የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ የወጣቶችን ጉዳይ በሁሉም ዘርፎች ውስጥ ለማካተት የሚያስችል የምክክር መድረክ በወራቤ ከተማ ተካሂዷል። የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ኃላፊ አቶ ጌታቸው ሌሊሾ በመድረኩ ወጣትነት የፈጠራና የእውቀት ምንጭ በመሆኑ ወጣቶች በስነ-ምግባር ታንጸው ለሀገር እድገት የበኩላቸውን እንዲወጡ በትኩረት እንደሚሰራ ገልጸዋል። 

የማካተቻ ጋይድ ላይን ወጣቱን ወደ ልማት ማዕቀፍ ለማምጣት እንደ ትልቅ መሣሪያ እንደሚያገለግል አስታውቀዋል። ወጣቱ የሀገሪቱ ዋነኛ አምራች ኃይል እንደመሆኑ መጠን ጉዳዩ በአንድ ተቋም ብቻ ተይዞ የሚታለፍ ሳይሆን በሁሉም ሴክተር መሥሪያ ቤቶችና የልማት ድርጅቶች ውስጥ ትኩረት ሊሰጠው የሚገባ መሆኑንም አሳስበዋል። 

አቶ ጌታቸው የማካተቻ ጋይድ ላይን ዋና ዓላማ ወጣቶች በሁሉም የልማት ፖሊሲዎችና ፕሮግራሞች ውስጥ እኩል የመልማትና የመጠቀም እድል እንዲኖራቸው ማድረግ፤ በመንግሥታዊና መንግሥታዊ ባልሆኑ ድርጅቶች ውስጥ የወጣቶች ጉዳይ ቅድሚያ የሚሰጠው አጀንዳ እንዲሆን ሁኔታዎችን ማመቻቸት ብሎም ለፖሊሲ አውጪዎችና ለእቅድ ባለሙያዎች እንደ ማጣቀሻ ሰነድ ሆኖ እንዲያገለግል ማድረግ መሆኑን አመላክተዋል። 

ኃላፊው እስከ መጋቢት 30 ቀን 2018 ዓ.ም ድረስ ልዩ ትኩረት ተሰጥቷቸው የሚከናወኑ ሶስት ዋና ዋና ተግባራትን አብራርተዋል፡- የዲጂታል መታወቂያ ምዝገባ፡ ወጣቶችን ወደ ዘመናዊው የዲጂታል ሲስተም በማስገባት ተጠቃሚነታቸውን ማሳደግ፤ የኢትዮ ኮደርስ (5 Million Coders) ስልጠና፡ የቴክኖሎጂ ባለቤት የሆኑ ወጣቶችን ለማፍራት የቀረበውን እድል የመጠቀም እንዲሁም የወጣቶች የስብዕና ማዕከላቱን በማጠናከር ወጣቶች ከመደበኛው ትምህርት ጎን ለጎን እውቀትና ክህሎት እንዲያገኙ ማድረግ እስከ መጋቢት 30 ድረስ በልዩ ትኩረት ማጠናቀቅ እንደሚገባ አሳስበዋል። 

የቢሮው ምክትል ኃላፊ እና የወጣት ዘርፍ ኃላፊ አቶ ሱልጣን አሊ በበኩላቸው ወጣቶች በፖሊሲ ቀረጻና በውሳኔ ሰጪነት ሂደቶች ላይ ያላቸው ተሳትፎ ተቋማዊ አሰራር እንዲኖረው ለማድረግ ቢሮው በትኩረት እየሰራ መሆኑን ገልጸው፤መድረኩ ለወጣቱ ሁለንተናዊ ብቃት እንዲሰሩ የሚያስችል ግንዛቤ የሚፈጥር መሆኑን ጠቁመዋል። የወጣቶችን ጉዳይ በተለያዩ የመንግሥትና የግል ተቋማት ውስጥ ተቋማዊ በሆነ መንገድ ማካተት የወጣቱን ተሳትፎ እና ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ወሳኝ መሆኑ ተናግረዋል። 

ኢትዮጵያ የፈረመቻቸውን የአፍሪካ ወጣቶች ቻርተር እና የሀገሪቱን የወጣቶች ፖሊሲ መሰረት በማድረግ የተዘጋጀው አዲስ ጋይድ ላይን፤ ወጣቶች በፖሊሲ ቀረጻ፣ በፕሮጀክት ዲዛይን እና በትግበራ ሂደቶች ውስጥ ቀጥተኛ ተሳታፊ እንዲሆኑ እንደሚያስችል አስታውቀዋል። በተለይም የወጣት ኃይል፤ በኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊና ፖለቲካዊ መስኮች ላይ ያለውን ክፍተት ለመሙላት መመሪያው ትልቅ ፋይዳ እንደሚኖረው በመድረኩ ላይ ተገልጿል። 

በመድረኩ ላይ ከክልል፣ ከዞን፣ ከልዩ ወረዳ እና ከከተማ አስተዳደር የወጣቶችና ስፖርት ቢሮ መምሪያና ጽህፈት ቤት ኃላፊዎችና የወጣት አደረጃጀቶች የተሳተፉ ሲሆን፣ የተጀመሩ የልማትና የዲጂታል ንቅናቄ ስራዎችን በላቀ ውጤት ለማጠናቀቅ የጋራ መግባባት ላይ ተደርሷል።