Skip to main content
youthnews7

በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ወጣቶችን በምግብ ስርዓት ማጠናከሪያ ፕሮግራም ተጠቃሚ ለማድረግ እየተሰራ እንደሚገኝ ተገለጸ። 

(ሆሳዕና፤ መጋቢት 1/2018) በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የወጣቶችን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የሚያስችሉ ፖሊሲዎች፣ ፕሮግራሞችና ልዩ ልዩ ፓኬጆች ተነድፈው ተግባራዊ እየተደረጉ መሆኑን የክልሉ ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ አስታውቋል። 

የቢሮው ምክትልና የወጣት ዘርፍ ኃላፊ አቶ ሱልጣን አሊ በሀላባ ቁሊቶ ከተማ በተካሄደ የውይይት መድረክ ላይ እንደገለጹት፤ መንግስት የወጣቶችን ተሳታፊነት የሚያረጋግጡ ፖሊሲዎች፣ ፕሮግራሞችና ልዩ ልዩ ፓኬጆች ቀርጾ እየሰራ ይገኛል። በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ወጣቶችን በምግብ ስርዓት ማጠናከሪያ ፕሮግራም ተጠቃሚ ለማድረግ እየተሰራ እንደሚገኝ አቶ ሱልጣን ተናግረው፤ "የምግብ ስርዓት ማጠናከሪያ ፕሮግራም" (FSRP) ተጠቃሽ መሆኑን ኃላፊው ገልጸዋል። አቶ ሱልጣን አክለውም፣ በክልሉ ካለው ከፍተኛ የወጣት ቁጥርና ፍላጎት አንጻር፣ መሰል ወጣቶችን ወደ ስራ የሚያስገቡና ተጠቃሚ የሚያደርጉ ፕሮግራሞች በስፋት ሊበራከቱ እንደሚገባ አሳስበዋል። 

በክልሉ ግብርና ቢሮ የበምግብ ስርዓት ማጠናከሪያ ፕሮግራም ስራ አስኪያጅ አቶ ከድር መሃመድ በበኩላቸው፣ ፕሮግራሙ በክልሉ በ4 ዞኖች በሚገኙ 10 ወረዳዎችና 289 ቀበሌዎች ተግባራዊ እየተደረገ መሆኑን ገልጸው፤ ከ1 ነጥብ 1 ሚሊዮን በላይ አርሶ አደሮችን በቀጥታ ተጠቃሚ የሚያደርግ ፕሮግራም እንደሆነ ተናግረዋል። በዚህ ወቅት ፕሮግራሙ በግብርና አገልግሎት አሰጣጥ፣ ተጋላጭነትን የሚቋቋም መስኖ ልማት፣ በገበያ ስርአት እና አቅም ግንባታ ላይ እየሰራ ይገኛል ብለዋል። 

በኢንተርፕራይዝ ልማት፣ የግብርናና መሰረተ ልማት እና በአቅም ግንባታ በመስኖ ልማት ወጣቶችን ተጠቃሚ የሚያደርጉ በርካታ ስራዎች መከናወናቸውን ገልጸዋል። እንደ አቶ ከድር ገለጻ፣ ፕሮግራሙ የክልሉን የግብርና ኢኒሼቲቮች በተለይም የ 30-40-30 የፍራፍሬ (አፕል፣ አቮካዶ፣ ሙዝ እና ፓፓያ) ልማትን በልዩ ትኩረት እየደገፈ ይገኛል። 

በፕሮግራሙ የምርትና ምርታማነት ማደግ እንዲሁም የማህበረሰቡ የአመጋገብ ባህል መሻሻል የተገኙ የውጤት ማሳያዎች መሆናቸውን ተናግረዋል። በመድረኩ ወጣቶችን በፕሮግራሙ ውስጥ ማካተት የሚያስችል መመሪያ ሰነድ ቀርቦ ውይይት የተደረገበት ሲሆን፣ የጋራ መግባባት ላይም ተደርሷል። ለዞንና ለወረዳ የዘርፉ ባለሙያዎችና ባለድርሻ አካላት በአቶ ሱልጣን አሊ ቀጣይ የስራ መመሪያ ተሰጥቶ መድረኩ ተጠናቋል።