AdminYouthsport
በ3ኛው የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ልዩ ልዩ ሻምፒዮና እና የባህል ስፖርቶች ፌስቲቫል ላይ በድምር ውጤት የሁለተኛነት ደረጃን ያስመዘገበው የሀዲያ ዞን ልዑክ ቡድን ሆሳዕና ከተማ ሲገባ ደማቅ አቀባበል ተደረገለት።
20/06/2018 (ዱራሜ)
በ2ኛው ሻምፒዮና ላይ አንደኛ ደረጃን ይዞ አጠናቆ የነበረው የዞኑ ልዑክ፤ በ3ኛው ውድድር በ10 የባህል እና በ17 የዘመናዊ ስፖርት አይነቶች፣ በድምሩ በ27 የስፖርት አይነቶች ከ250 በላይ ስፖርተኞች አሳትፎ እስከመጨረሻው የሚዘልቅ ብርቱ ፉክክር አድርጓል።
ቡድኑ የአንደኛነት ክብሩን ለማስጠበቅ ከፍተኛ ጥረት ቢያደርግም፣ በክልሉ ዞኖች መካከል በነበረው ከፍተኛ ፉክክር በአጠቃላይ የሁለተኛነት ደረጃን ይዞ አጠናቋል።
በሆሳዕና ከተማ በተከናወነው ደማቅ አቀባበል ላይ የተገኙት የሀዲያ ዞን ወጣቶችና ስፖርት መምሪያ ኃላፊ አቶ ታምሬ ኤርሚያ እንደተናገሩት፤ ቡድኑ በሁሉም የስፖርት አይነቶች የተሻለ ተሳትፎ ለማድረግ ጥረት ማድረጉን ገልጸዋል።
ሰፊ ተሳትፎ ባልነበረበት ሁኔታ እንዲህ ያለ ስኬት ማምጣት እንደማይቻል የገለጹት ኃላፊው፣ ለዚህ ውጤት መገኘት የዞኑ አስተዳደር ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማድረጉን ጠቅሰዋል።
አክለውም ሁሉም የከተማ ከንቲባዎችና የወረዳ አስተዳዳሪዎች ከዞኑ አስተዳደር ልምድ በመውሰድ በየአካባቢያቸው ያሉትን ውስንነቶች መቅረፍ እንዳለባቸውና በወጣቶች ላይ መስራት ትልቅ ትርጉም እንዳለው አሳስበዋል።
የመምሪያው ምክትልና የስፖርት ዘርፍ ኃላፊ አቶ ክብሩ ዮሐንስ በበኩላቸው፤ ልዑኩ ከመነሻው ታቅዶ እንደሄደው በውድድሩ ላይ በደማቅ ሁኔታ መሳተፍ መቻሉን ገልጸዋል።
በሁሉም የውድድር መድረኮች ሀዲያ በከፍተኛ ብቃትና ውጤት ተሳታፊ እንደነበረ የገለጹት ኃላፊው፤ ምንም እንኳን ከዕቅድ አንፃር የቀሩ ውጤቶች ቢኖሩም በ27ቱ የስፖርት አይነቶች ተሳትፎ በማድረግ 17 ዋንጫዎችን ማሳካት መቻሉን ተናግረዋል።
በመጨረሻም በውድድር ስፍራው የነበረው ቆይታም እጅግ ያማረና ስኬታማ እንደነበር ጠቁመዋል።